በካናዳ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ22ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – በካናዳ ሰስካቹዋን ግዛት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ22ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰብስቧል፡፡
በካናዳ የሚገኘው የጥምረት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሰስካቹዋን ፕሮቪንስ ቻፕተር በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የቨርቹዋል ኮንፈረንስ እና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከ12ሺህ ዶላር በላይ ነጻ ድጋፍ የተደረገ እና ቃል የተገባ ሲሆን፥ ከ10ሺህ ዶላር በላይ የቦንድ ግዢ በቀጥታ ከአገር ቤት ለመፈጸም ቃል ተገብቷል።
በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በካናዳ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፥ በአጠቃላይ በካናዳ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
በተጨማሪም የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀው፥ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካለችበት ውስብስብ ሁኔታ አንፃር ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በአገሩ ጉዳይ አርበኛ በመሆን የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ በካናዳ የጥምረት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃላፊ ዶክተር ፍሰሃ ሰለሞን፥ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት እምነት እንዳላቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡