በኬንያ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጅ ኬንያውያን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ

ሰኔ 20/2013 (ዋልታ) – በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሃግብር ላይ የኤምባሲው ሰራተኞች፤ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጅ ኬንያውያን በኤምባሲው ቅጥር ግቢ በመገኘት ችግኞችን ተክለዋል።

ኤምባሲው በመጀመሪያው ዙር በናይሮቢና አካባቢው ከሚገኙ ዳያስፖራ ማህበረሰብ ጋር በመሆን አንድ ሚሊየን ችግኞችን የሚተክል ሲሆን፤ እንዲህ አይነት መርሃ ግብሮች የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲ በማጠናከሩ ረገድ ሚናው ጉልህ እንደሚሆን በኬንያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የኬንያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ቀጠናውን ለማስተሳሰር እያደረገች ያለውን ጥረት አንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡
በሦስተኛው ዙር እና ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በመተባበር በምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኤምባሲው ከአስር ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ነው የተነሳው፡፡
ኤምባሲው በናይሮቢና አካባቢው ከሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመሆን በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በአገር ውስጥ የልማት ስራዎች ዙሪያ የጎላ ስራ ስለማከናወኑ ተነስቷል።
(በአስታርቃቸው ወልዴ)