መጋቢት 7/2015 (ዋልታ) በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን የክልሉ የሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በዘንድሮው ዓመት ለግድቡ ግንባታ 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኃይለሚካኤል ካሳሁን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት ከ15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀሙን ነው የገለጹት።
ባለፉት ዓመታት ግድቡን ከደለል ለመከላከል የክልሉ ህዝብ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በችግኝ ተከላ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።
እንደሀገር በተጀመረው 2ኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ ጉዞም ደብረ ማርቆስ እና ጎንደርን ጨምሮ በስምንት የክልሉ ከተሞች ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርግ ቅስቀሳ መደረጉን ገልጸዋል።
ለግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከመጋቢት 15 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ተጨማሪ ገንዘብ በቦንድ ግዥ ለማሰብሰብ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማፋጠን እየተደረገ ላለው ጥረት መላው የክልሉ ህዝብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኃላፊው ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።