ሰኔ 24/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽነትና የተጠቃሚውን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪጅን ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ መርኃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ፒኤችዲ) በመርኃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ለክልሉ ሕዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዛሬ የተዋቀረው ክልላዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሪጅን ጽሕፈት ቤቱ መቋቋምም በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታትና የተጠቃሚውን ቁጥር ለማሳደግ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ እንደገለጹት እየጨመረ የመጣው የኤሌክትሪክ ፍላጎት ካልተመለሰ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡
በክልሉ የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ ችግር በፍጥነት ለመፍታት በቅንጅት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
የተዋቀረው አዲሱ ክልላዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪጅን ጽሕፈት ቤት ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን እንደሚጀምር የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW