በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የሌማት ትርፋት ስራዎች የመስክ ጉብኝት ተደረገ

መጋቢት 29/2015 (ዋልታ) በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የሌማት ትርፋት ስራዎች የመስክ ጉብኝት ተደረገ፡፡

በመስክ ጉብኝቱ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ክልሉ ለግብርናና ለእንስሳት እርባታ ምቹ በመሆኑ ከመደበኛ አስተራረስ በተጨማሪ በበጋ መስኖና በሌማት ትሩፋት ንቅናቄዎች ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ በዘመናዊ አስተራረስና በመካናይዝድ ቴክኖሎጂ እንዲያለማ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት ክልሉ በበጋ መስኖ ልማት 50 ሺሕ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 3 ሺሕ 400 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።

በበጋ መስኖ በማልማት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአርሶ አደሩን የስራ ባህልና የበጋ መስኖ ላይ ያለውን አመለካከት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመስክ ምልከታው ወቅት ክልሉ በርካታ የበጋ መስኖና የግብርና ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው የሚደነቅ እንደሆነ ገልታ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለመጨመር በቴክኖሎጂ ለማገዝና በማዘመን ሚኒስቴሩ ከክልሉ ጋር በቅንጅት ይእንደሚሰራ አመልክተዋል።

በመስክ ምልከታው ጊንቦ ሀማና እና ዴሮ ውረዳን ጨምሮ በክልሉ ባሉ ወረዳዎች ላይ የተከናወኑ የበጋ መስኖና የሌማት ትሩፋት ስራዎች ተጎብኝተዋል።

 

ብሩክታይት አፈሩ (ከቦንጋ)