በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ማገዝ እንደሚገባ ተገለጸ

ሚያዝያ 6/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርናውን ዘርፍ በግብዓት አቅርቦትና በሜካናይዝድ መሳሪያ ማገዝ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በክልሉ በቤንች ሸኮ ዞን ለአከባቢው ስነ-ምህዳር የሚስማማ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በ500 ሄክታር ማሳ ላይ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ምክትል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አሸናፊ ክንፌ ሥራውን በቴክኖሎጂ በማገዝ እና በክልሉ የሚገኙ አምራች አርሶ አደሮችን የምርጥ ዘር አጠቃቀም በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንደ አገር የተጀመረውን የምግብ ዋስትና በክልሉ ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሳሙኤል አሰፋ ዞኑ የበቆሎ ምርትን በጥራት እንዲያመርት የዘር ብዜት እርሻን በሙሉ አቅም በማንቀሳቀስ ለክልሉ ሕዝቦችና አጎራባች ክልሎች ምሳሌ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የክምቴክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ኃላፊ ይመኑ ጀምበሬ መንግሥትና ባለሀብቱ ተቀራርበው መስራት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ በግብርናውም ይሁን በሌላ ዘርፎች የአገሪቱን ችግር መፍታት ይቻላል ብለዋል።

አክሊሉ ሲራጅ (ከቤንች ሸኮ ዞን)