ሰኔ 05/2013(ዋልታ) – በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ ላይ የሚደረግን ጫና መከላከል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኬንያና ማላዊ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር የህዳሴ ግድብ መሠረት የተጣላበት 10ኛ ዓመት በናይሮቢ አክብሯል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የመጀመሪያው የህዳሴ ግድብ ሙሌት ደስታን እንደፈጠረ አስታውጫ፣ ዳይሬክተሯ ሁለተኛው የግድቡ የውሃ ሙሌት የሀገሪቱን የመደራደር አቅም ከፍ የሚያደርግና ፍሬውንም የምንቀምስበት ነው ብለዋል፡፡
በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወሳኝ ወቅት ሀገሪቱን በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸው እና በዲኘሎማሲው መስክ አንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በህዳሴ ግድብ ሂደትና ድርድር ዙሪያ ማብራሪያ ያቀረቡት የግድቡ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ኘሮፌሰር ይልማ ስለሺ በበኩላቸው በግብጽ እና ሱዳን መንግስታት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት የተነሳ ድርድሩ መሳካት አልቻለም ብለዋል፡፡
በኬንያ ኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ግድቡን ማጠናቀቅ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ዜጐች ብሔራዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡