በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – 1 ሺህ 442ኛው የኢድ አል አድሐ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ጠዋት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚኖረው የጠዋት ስግደት ምክንያት አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የተወሰኑ መንገዶች ለጊዜው ለትራፊክ ዝግ ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ጠይቋል፡፡

በዚህም መሰረት፡-

ከመገናኛ እና ከ22 ለሚመጡ ኡራኤል አደባባይ፣ ከቦሌ ወደ መስቀል አደባባይ ኦሎምፒያ፣ ከሪቼ ወደ መስቀል አደባባይ የቀድሞ 4ኛ ክፍለ ጦር፣ ከጦር ኃይሎች ወደ ስታዲየም ሜክሲኮ አደባባይ፣ ከመርካቶ በበርበሬ በረንዳ በተክለ ሐይማኖት ወደ ስታዲየም ለሚመጡ ጥቁር አንበሳ ሼል፣ ከሞላ ማሩ በጌጃ ሰፈር ወደ ስታዲየም ለሚመጡ ጎማ ቁጠባ፣ ከፒያሳ ወደ ስታዲየም ለሚመጡ ቴዎድሮስ አደባባይ እንዲሁም ከ4 ኪሎ በፊት በር ወደ መስቀል አደባባይ ጊቢ ገብርኤል የሚወስዱ እና በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚገኙ መጋቢ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ ብሏል፡፡

ከዚህ አንጻርም አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ የተጠየቀ ሲሆን በተጠቀሱት መንገዶች ላይ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪን አቁሞ መሔድ የተከለከለ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪም እንደ ሁልጊዜው ለከተማዋ ሰላም ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ተባባሪ እንዲሆኑ የመጠየቁን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡