ሚያዝያ 1/2015 (ዋልታ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 518 ሚሊዮን ብር ከመዲናዋ ነዋሪዎች ድጋፍ መሰብሰቡን በአዲስ አበባ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት በማስመልከት ዛሬ በየካ ክፍለ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምስክር ነጋሽ ለግድቡ ግንባታ ስኬት የመዲናዋ ነዋሪዎች ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ከመዲናዋ ነዋሪዎች 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከመዲናዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 685 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 518 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት በማስመልከት በየካ ክፍለ ከተማ ድጋፍ የማሰባሰብ እና ሌሎች የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክፍለ ከተማው ምክትል ስራ አስፈጻሚ ፀሐይ ኪባሞ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ የህብረተሰቡ ድጋፍና ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በክፍለ ከተማው ህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከነዋሪዎች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ድጋፉ የተሰበሰበው ከነዋሪዎች፣ ከተቋማት፣ ከባለሃብቶችና ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መሆኑን ጠቅሰዋል።