ከንቲባዋ በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወነ መሆኑን ገለጹ

ሚያዝያ 1/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው በከተማዋ የጀመርናቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከፊሎቹን ዛሬ ጎብኝተናል ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም በህዝብ ጥያቄ የተጀመሩ ዘመናዊ ሆስፒታሎች፣ የከተማዋ የግብርና ምርት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ወሳኝ ሚና ያላቸው የገበያ ማዕከላት፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለምርት አቅርቦት ትልቅ ሚና ያለው የኢንዱስትሪ ክላስተር እና የመንገድ ፕሮጀክቶች መጎብኘታቸውን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም የአመራሮችን ብቃት ለመገንባት የሚያግዝ አካዳሚን ጨምሮ የሌሎች ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

መጀመር ብቻ ሳይሆን በጊዜ የማጠናቅቅ ልማዳችንን በማጠናከር ፕሮጀክቶቻችን በተያዘላቸው ጊዜ እና በተመደበላቸው በጀት በጥራት ግንባታቸው እየተፋጠነ ይገኛል ያሉት ከንቲባዋ ፕሮጀክቶቹ የከተማችንን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያቀለጣጥፉ፣ የህዝቡን የኑሮ ሸክም የሚያቀሉ፣ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንዲሁም የከተማችንን ገጽታ የሚያሻሽሉ ናቸው ብለዋል።

የከተማችንን ነዋሪዎች በታማኝነት እና በትጋት ለማገልገል የገባነውን ቃል በተግባር እንድንፈጽም የደገፋችሁን ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ሲሉም አክለዋል።