በየብስ ከሚደረገው የኮንትሮባንድ ዝውውር በተጨማሪ በአየር መንገድ በኩል የሚከናወነው ኮንትሮባንድ ይበልጥ አሳሳቢ መሆኑ ተገለፀ

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ) በየብስ ከሚደረገው የኮንትሮባንድ ዝውውር በተጨማሪ በአየር መንገድ በኩል የሚከናወነው የኮንትሮባንድ ዝውውር ችግሩን የበለጠ አሳሳቢና ውስብስብ እንዲሆን እንዳደረገው የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በመከላከልና በመቆጣጠር በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በቅንጅት የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ የሚገመግም የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡

በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ በሃገር ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመመከት ኮሚሽኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተሰሩት ቅንጅታዊ ስራዎችም በኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ሐገር ልታጣ የነበረውን ከ84 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን እንደ ተቻለ ጠቁመዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተገኔ ደረሰ በበኩላቸው ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የአካልና የህይወት መስዋዕትነት እየተከፈለ መሆኑን አስረድተዋል።

በየብስ ከሚደረገው የኮንትሮባንድ ዝውውር በተጨማሪ በአየር መንገድ በኩል የሚከናወነው የኮንትሮባንድ ዝውውር ችግሩን የበለጠ አሳሳቢና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታልም ብለዋል፡፡

በዚህም በ2015 የበጀት ዓመት በኤር ፓርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብቻ ከ2.8 ቢሊየን ብር በላይ የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም ባለፈው የበጀት ዓመት 11.6 ቢሊዮን ብር የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችንና በድርጊቱ የተሳተፉ 1 ሺሕ 393 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና የፍትህ ሚኒስቴር እየተሳተፉበት እንደሚገኝ ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡