በዩኒቨርሲቲው ስር የሚገኘው የካንሰር ማዕከል በአርቲስት አሊ ቢራ ስም ተሰየመ

አርቲስት አሊ ቢራ

መስከረም 30/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀረር ከተማ የሚገኘው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ማዕከል በአርቲስት አሊ ቢራ ስም ተሰየመ።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አርቲስት አሊ ቢራ ህይወቱ አስኪያልፍ ድረስ ስለሰው ልጆች መብትና ፍቅር የኖረና የደግነት ምልክት ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ያለውን ሲያካፍል የኖረ አርቲስት መሆኑን አስታውሰው አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር የራሱን አስተዋጽኦ ያደረገ ለሌሎችም በአርዓያነት የሚጠቀስ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የካንሰር ማዕከሉ የአርቲስቱን ጥንካሬ በሚመጥን መልኩ አገልግሎት መስጠት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል ዩሱፍ (ዶ/ር) አርቲስት አሊ ቢራ ለኦሮሞ ህዝብ እና ለመላው ብሔር ብሔረሰቦችና የኖረ የጥበብ ሰው መሆኑን አስታውሰዋል።

ማዕከሉ በአርቲስቱ ስም መሰየሙም ከካንሰር ህመም ጋር በተያያዘ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን የአመለካከት ክፍተት ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)