በደቡብ ክልል ከ971 ሚሊየን በላይ  ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር ከ971 ሚሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለጸ።

በተያዘው አመት ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥም ከ25 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት በጎረቤት  ሀገራት የሚተከሉ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አስመልክቶ በጉራጌ ዞን የመስክ ምልከታ ተደርጓል።

በወቅቱም በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በክልሉ ከ971 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ማዘጋጀት እንደተቻለ ተናግረዋል።

የፍራፍሬ የእንስሳት መኖ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞችን ማዘጋጀት ተችሏል ያሉት አቶ አንተነህ፣ የዝናቡን ስርጭት በመከታተል ለአካባቢ እንክብካቤ ልማት ስራው ስኬታማነት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ በበልግ እና በመኸር የአዝመራ ወቅት የአረንጓዴ አሻራን ተግባራዊ ለማድረግ የችግኝ ዝግጅት እና የጉድጓድ ቁፋሮ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር የአፈር መሸርሸር እንዳይከሰት ከማድረግ ባሻገር የከርሰ ምድር የውሀ መጠን እንዲጨምር እያደረገ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የችኝኝ ዝግጅት ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ውስጥ አንዱ የጉራጌ ዞን መሆኑን የተናገሩት ሀላፊው፣ በዘርፉ እየተካሄደ ያለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ውጤታማ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት እንደተቻለም ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራን መርኃግብር  ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለኬንያና ለደቡብ ሱዳን ድጋፍ ለማድረግ  ታቅዷል ማለታቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።