የኮቪድ-19 ጥንቃቄ መስፈርቶችን ላሟሉ ሆቴሎች እውቅና ተሰጠ

ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – በሲዳማ ብሔራዊ ክልል የኮቪድ-19 ጥንቃቄ መስፈርቶችን ላሟሉ ሆቴሎች እውቅና ተሰጠ፡፡

በኮቪድ-19 ፕሮቶኮል የመከላከልና የጥንቃቄ መመሪያው ከተካተቱት ውስጥ አንዱ በሆቴል ዘርፍ በመሆኑ በሲዳማ ብሔራዊ ክልል የኮቪድ-19 ጥንቃቄ መስፈርቶችን ላሟሉ ሆቴሎች የእውቅና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መሰጠቱን የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሲዳማ ብሔራዊ ክልል 22 ባለኮከብ ሆቴሎች ውስጥ 21ዱ የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን በአገልግሎት አሰጣጣቸው ውስጥ የጥንቃቄ መስፈርቶችን ተግባራዊ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም የተቀመጡትን ዝርዝር መስፈርቶች አሟልተው በመገኘታቸው የእውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል።

የእውቅና አሰጣጡ እና የግምገማ ሂደቱ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ባለሙያዎች እና ከሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ የተሰራ ሲሆን፣ ቀጣይነት ያለው እና ተሞክሮ የተወሰደበት እንደሆነ መገለፁን ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡