በደጊት ጥብቅ ደን  የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ደጊት ጥብቅ ደን

መጋቢት 18/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ “ደጊት” ጥብቅ ደን የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደመቀ አድማሱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣  የእሳት ቃጠሎው  በወረዳው 018 ቀበሌ  በሚገኘው “ደጊት” ጥብቅ ደን የተነሳው ትናንት ከሰዓት በኋላ  ነው።

የአካባቢው መልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ ወጣ ገባ፣ ተራራማ መሆኑና ተቀጣጣይ ሳር በውስጡ የበዛበት በመሆኑ እሳቱን ለማጥፋት ፈታኝ እንዳደረገው ገልጸዋል።

ይህም ሆኖ የአካባቢውን ሀብረተሰብ አስተባብሮ በማሳተፍ የእሳት ቃጠሎው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በጥብቅ ደኑ ሀገር በቀል እጽዋትና የተለያዩ የዱር እንስሳት  የሚኖሩበት መሆኑን  ጠቁመው፤ ጉዳት እንዳይደርስባቸው  እሳቱን የማጥፋት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የቃጠሎው መንስኤ እየተጣራ ቢሆንም ከከሰል ማክሰል ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ነው ሃላፊው የጠቆሙት።

“ደጊት” ጥብቅ ደን ከ60 ሄክታር መሬት በላይ እንደሚሸፍን ተመልክቷል፡፡