በዳንሻ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ

መጋቢት 25/2014 ( ዋልታ) በዳንሻ ከተማ አስተዳደር “ለአሸናፊነት እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ የከተማውን ማኅበረሰብ ያሳተፈ የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።
ሩጫው በፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኀበር አስተባባሪነት የተካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ደመላሽ አበበ ሩጫው የፋሲል ከነማን በመደገፋቸውና የክለቡን ማሊያ በመልበሳቸው ብቻ በትሕነግ የታሠሩ፣ ግፍና መከራ የደረሰባቸው ወገኖችን ለመዘከር ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በጎዳና ላይ ሩጫው ደረጃ ለያዙ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት መበርከቱን አሚኮ ዘግቧል።
በቀጣይም ደጋፊዎችን በማስተባበር በስፖርቱ ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማኅበሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።