ኢሶዴፓ አገራዊ ምክክር ከግብ እንዲደርስ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገለፀ

መጋቢት 24/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አገራዊ ምክክር ከግብ እንዲደርስ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገለፀ።
ፓርቲው ይህን ያለው ዛሬ እያካሄደ ባለው 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ነው።
የኢሶዴፓ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) አገሪቱ ከኋላቀር የፖለቲካ አካሄድ ወጥታ የዴሞክራሲ መንገድ እንድትከተል ሰላማዊ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።
የዜጎች ሰብኣዊ መብት እንዲከበርና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚቀጥልበትም ገልጸዋል።
በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ከማዕከላዊነት ወጥቶ እስከታችኛው መዋቅር እንዲደርስና በተለይ አሁን ላይ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ምክክር ግቡን እንዲመታ ፓርቲው የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
በፓርቲው ጉባኤ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የኢሶዴፓ ምክትል ሊቀመንበርና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሄል ባፌ (ዶ/ር)፣ የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ፣ ከእናት ፓርቲ ሰይፈስላሴ አያሌው እና የሌሎችም የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ተገኝተዋል።
ከመጠላለፍና ከመገፋፋት ፖለቲካ ወጥተን ለአንድ አገር በጋራ መስራታችንን ልንቀጥል ይገባል ያሉት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮቹ ኢሶዴፓ የሰላማዊ ትግል አርዓያ መሆኑን በመግለፅ ጉባኤው ለአገር የሚበጅ አቅጣጫ የሚቀመጥበት ይሆናል በሚል ምኞታቸውን ገልፀዋል።
ኢሶዴፓ በጉባኤው ባለፉት አምስት ዓመታት ፓርቲው ያሳካውንና የገጠሙትን ፈተናዎች የሚገመግምበት ነው።
ከዚህ ባለፈም የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመተዳደሪያ ደንብ ማፅደቅ እና የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫንም ያከናውናል ተብሏል።
በትዕግስት ዘላለም