በድሬዳዋ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ላደረገው አስተዋጽኦ ኮሚሽኑ ምስጋና አቀረበ

ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ላደረገው አስተዋጽኦ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋና አቀረበ።

በከተማ አስተዳደሩ ዛሬ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ ውጤት ለህዝብ ይፋ መደረጉን በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ አስታወቋል።

የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ እንደገለጹት፣ የድሬዳዋ ፖሊሶች፣ ለምርጫው የተዋቀረው የፍትህና የፀጥታ ተቋማት ምክር ቤት ተቀናጅተው ለምርጫው መሳካት ከፍተኛ ሥራ አከናውነዋል።

በተለይ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅትም ፖሊስ ከየምርጫ ጣቢያዎቹ የምርጫ ቁሶቹ ደህንነት እየጠበቁ መሆኑን ጠቁመው፣ የሚገኘውን ጊዜያዊ ውጤት ተከትሎ በድህረ ምርጫ የሚነሱ ጥያቄዎች ካሉ በህጉ-መሰረት መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን በበኩላቸው በአስተዳደሩ ምርጫው በስኬት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ በምርጫ ላይ ላደረገው የነቃ ተሳትፎ አመስግነዋል።

በድሬዳዋ ትናንት የተካሄደው ምርጫ በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ በተቋቋሙ ምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን በመጠቆም፤ ዛሬ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ ውጤት ለህዝብ ይፋ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በምርጫው ላይ እስካሁን የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩንም አስታውቀዋል።