በድሬዳዋ ከ350 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 4 አምራች ኢንዱስትሪዎች ተመረቁ

ሐምሌ 19/2015 (ዋልታ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከ350 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 4 አምራች ኢንዱስትሪዎች ተመረቁ፡፡

ለምረቃ የበቁት ሙይ የማዳበሪያ ከረጢት ማምረቻ፣ ሀምዲያ ዱቄት ፉብሪካ፣ ጎጆ የቤት ክዳን እና ዳይመንድ ሚስማር ፉብሪካ እንዲሁም ኤችኦኤች የመኪና መገጣጠሚያ እና የቦዲ ስራ ፉብሪካዎች ናቸው።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በምረቃው ወቅት እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ 10 የማምረቻ ፉብሪካዋች ተመርቀው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በቀጣይ ወደ ስራ ሲገቡ ከመብራት መቆራረጥ፣ ከውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ከማስፋፊያ ጋር በተያያዘ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ባለሀብቶች እና ተወላጆች ወዳጆች በልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአስተዳደሩ በ2015 በጀት አመት ከ34 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ካፖታል ያስመዘገቡ 214 የሚሆኑ ባለሀብቶች መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

የፉብሪካ ባለቤቶች በበኩላቸው የመሰረተ ልማት አለሟላት፣ የመብራት መቆራረጥ በምርታማነታቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው በመግለፅ በቀጣይ ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል፡፡

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ ከንቲባ ከድር ጆሀርና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በፋብሪካዎቹ ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራ ማኖራቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡