በድሬዳዋ 2 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

ግንቦት 24/2014 (ዋልታ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 2 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታውቀ፡፡

ከዚህ ውስጥ 200 ሺሕ ችግኞች በጎረቤት ሀገር ጅቡቲ እና የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በአጎራባች ወረዳዎች የሚተከሉ መሆናቸው ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢሊያስ አልይ በአስተዳደሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 4 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን እና ከተተከሉ ችግኞች መካከልም 60 በመቶው መፅደቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በመርኃ ግብሩም ባለፉት ዓመታት የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍ የሚተከሉ ችግኞች ቁጥር እና የፅድቀት መጠን ማሻሻል መቻሉን ጠቁመው በዘንድሮ ዓመት በሚካሄደው አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 2 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

በአስተዳደሩ ከሚተከሉ ችግኞች መካከልም 40 በመቶው ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መሆናቸውንም ነው ምክትል ኃላፊው የጠቆሙት፡፡

የሚተከሉ ችግኞችን ከማዘጋጀት ባለፈ የተከላ ቦታዎች የመለየትና ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

መርኃ ግብሩ ቅንጅታዊ አሰራረን ያጎለበተና የይቻላል መንፈስ መፍጠሩንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የችግኝ ጣቢያ ባለሙያዎችም ፓፓያና ዘይቱናን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎችና የዛፍ ችግኞችን በማፍላት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመው ኅብረተሰቡም የሚተክላቸው ችግኞች እንዲፀድቁ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ተስፋዬ ኃይሉ (ከድሬዳዋ)