በጂቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ

በጂቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢፌዲሪ መንግስት ህግን ለማስከበር እና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ በሕወሓት ጁንታ ላይ የሚያካሄደውን ዘመቻ በስኬታማነት እየተወጣ ለሚገኘው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ሙሉ ደመወዛቸውን እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች፣ የሆቴል እና የሱቅ ባለቤቶች፣ በጂቡቲ የወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት፣ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ማህበራት ተወካዮች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ድጋፍ ባደረጉባቸው መድረኮች የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ ሰላምና ፀጥታ ያላቸውን የማይተካ ሚና አውስተው መንግስት ለሚያደርጋቸው አገራዊ ጥሪዎች ሁሉ አስፈላጊውን ለማበርከት ቃል ገብተዋል።

በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እገዛውን ላደረጉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት ስም ልባዊ ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።