በጅማ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ 6 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ንብረት ወደመ

Image may contain: one or more people and outdoor

 

በጅማ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ 6 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ የወረዳ ሁለት ጽህፈት ቤት ዋና አዛዥ ኮማንደር ካሊድ አባ ተማም አደጋው የደረሰው ዛሬ ንጋት አካባቢ 11 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማው በቦቾ ቦሬ ቀበሌ መናኸሪያ አካባቢ በሚገኝ በሚገኝ አንድ  የእንጨት ስራ ወጤቶች ማምረቻና መሸጫ የግል ድርጅት ላይ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።

በአደጋው በድርጅቱ ተመርተው ለገበያ የተዘጋጁ ዘመናዊ የእንጨት ስራ ውጤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን አመልክተዋል።

“የወደመው ንብረት 6 ሚሊየን ብር ግምት አለው” ያሉት ኮማንደር ካሊድ በአደጋው በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።

በአካባቢው ነዋሪዎች፣ በጸጥታ አካላትና በእሳት አደጋ መከላከያ ሰራተኞች ትብብር በተደረገ ጥረት ቃጠሎው ወደ ሌሎች የንግድ ተቋማት ሳይዛመት በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሆነ ኮማንደር ካሊድ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።