በጉለሌ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ተበረከተ


መስከረም 20/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በጉለሌ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች 14 ቤቶችን ገንብቶ አስረከበ።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ዘሪሁን አባተ ቤቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅና የቤት እቃዎችን ለማሟላት 31 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል ።

እስካሁንም የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ባለፉት አራት አመታት ከ70 በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች የቤት እድሳትና ግንባታ ማከናወኑን ገልጸዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎፍቃድ ማስተባበርያ ኮሚሽነር አብርሀም ታደሰ በዛሬው ዕለት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተላለፈውን 14 ቤቶች ጨምሮ 203 ቤቶች ለአቅመ ደካማዎች ተገንብተው በከተማ ደረጃ ተላልፈዋል ብለዋል።

የበጎፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ በ2015 1ሺሕ 899 ቤቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል ብለዋል ።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወልዴ ወገሴ በክፍለ ከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል ዘረፈ ብዙ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዛሬው እለት ቤት የተረከቡ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በማይመች ሁኔታ ይኖሩ እንደነበርና ቤታቸውን ለማደስም አቅም የሌላቸው በመሆኑ ችግር ውስጥ መቆየታቸውን አስታውሰው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመስከረም ቸርነት