በጉራጌ ዞን በ550 ሚሊየን ብር የሚገነባው የማይኒንግ ፋብሪካ መሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ሰኔ 23/2014 (ዋልታ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው እና የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ በጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ በ550 ሚሊየን ብር ለሚገነባው የኒው ኢራ ማይኒንግ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ አኖሩ፡፡

የኒው ኢራ ማይኒንግ ፋብሪካ በመጀመሪያ ዙር ለሀገር ውስጥ ምርት የሚሆን ግብአት እንደ ብርጭቆ ሴራሚክ፣ ለግንባታ ግብአት የሚሆኑ ቁሶችን የሚያመርት ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ፍሊንት ስቶን፣ ሶላር ፓናሎች እና መሰል ማዕድናትን ማምረት የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል።

ፋብሪካው ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ምርቶቹን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚያስችልም ተገልጿል፡፡

ፋብሪካውን ከአንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን እና ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ለ200 ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡