በጋምቤላ ክልል ዘመናዊ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል ተመረቀ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አካል የሆነውና ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ውጪ የተደረገበት ዘመናዊ የቁም እንስሳት የግብይት ማዕከል በጋምቤላ ክልል ተመረቀ።
በክልሉ ላሬ ወረዳ የተገነባው ማዕከል በ5 ሺሕ 625 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በውስጡ የመቆጣጠሪያ ኬላ፣ ሕመም ያለባቸው እንስሳት ለይቶ ማቆያ፣ የውሃ ማጠጫ ገንዳና የእንስሳት ማውረጃ መጫኛ ይዟል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ማዕከሉ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበረውን የቁም እንሳስት የግብይት ችግር እንደሚያቃልል ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት አራት ተመሳሳይ ማዕከላት ለመገንባት የተጀመሩ እንስቃሴዎች የክልሉን የቁም እንስሳት ግብይት በማዘመን አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ፕሮጀክቱ ለጀመራቸው የልማት ሥራዎች ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
የጋምቤላ ክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኦኬሎ ኡቦንግ የተገነባው ማዕከል የቁም እንስሳት ግብይት ውስጥ ያለውን የደላላ ጣልቃ ገብነትና የስርቆት ወንጀል ለማስቀረት አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የአካባቢው አርብቶ አደሮች በበኩላቸው የማዕከሉ መገንበት ቀደም ሲል ለቁም እንስሳት ግብይት ወደ ጋምቤላ ከተማ ያደረጉት የነበረውን የ80 ኪሎ ሜትር መንገድ እንደሚያስቀርላቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በጋምቤላ ክልል በስምንት ወረዳዎች እየተተገበረ ለሚገኘው የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ለ2014 ዓ.ም 470 ሚሊዮን ብር መመደቡ ተገልጿል።
በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍና በቆላና መስኖ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው ፕሮጀክት ጋምቤላን ጨምሮ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን ያካተተ ነው።
ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ 451 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦለታል።