በጎረቤት ሀገራት የችግኝ ተከላን በተመለከተ ለአምባሳደሮች ገለጻ ተሰጠ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በጎረቤት አገራት ችግኝ ለመትከል በተያዘው ዕቅድ ዙሪያ ተቀማጭነታቸውን በጎረቤት ሀገራት ላደረጉ ለኢ.ፌ.ዲ.ረ አምባሳደሮች በበይነ መረብ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ለሶስተኛ ጊዜ 6 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል የተያዘው የአረንጓደ አሻራ መርኃግብር የክልል ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማስጀመራቸውን አስታውሰው፣ በያዝነው ዓመት 1 ቢሊየን ችግኝ በጎረቤት ሀገራት ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎረቤት ሀገራት የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ከአገራት ጋር በኢኮኖሚ፣ በሰላም፣ የህዝብ ለህዝብ እና የመንግስታት ግንኙነትን ለማጠናከር እና የፓን አፍሪካዊነት ለማሳየት የአረንጓደ ልማት ትብብር በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን አቶ ደመቀ አስረድተዋል፡፡

በየአገራት የሚተከሉ ችግኞች የአገራቱን ሥነ ምህዳር እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ታሳቢ ያደረጉ  መሆናቸውን  በማረጋገጥ፣ እያንዳንዱ ሚስዮን የሚመለከታቸውን መሥሪያ ቤት ቀርቦ የፍላጎት እና የድርጊት መርኃግብር መረጃ አንዲያሳውቅ እንዲሁም ችግኞቹ ከተተከሉ በኃላ  ክትትል የሚደረግበት ሥረዓት እንድዘጋጅ  ለአምባሳደሮቹ  መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

የችግኝ ተከላው ስኬታማ እንዲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የአከባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች  መሥሪያ ቤቶች በቅንጅት እንደሚሰሩ አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

የችግኝ ተከላውም የአገራቱን ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች፣ በአገራቱ ነዋሪ የሆኑ የዳያስፖራ አባላት እና ሌሎች የሚመለከታቸው በተሳተፉበት በይፋዊ ሥነ ሥርዓት የሚጀመር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አምባሳደሮች የችግኝ ተከላውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ በየአገራት ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር ውይይት በማድረግ ለዕቅዱ ስኬታማነት ወደ ሥራ መግባታቸውን አመላክተዋል፡፡