በጥምቀት በዓል ያለፈቃድ ድሮን መጠቀም አይቻልም – የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን ለመላከል ከሚመለከተው አካል ፈቃድ የሌላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ድሮን ማብረር ወይንም ማንቀሳቀስ እንደማይችሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ሁሉም የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ከከተራ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በድምቀት የሚከበረዉ የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት አድርገዋል።

ከፀጥታ አጠባበቅ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከልም የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል።

ከተገቢው አካል ፈቃድ ሳይኖራቸው ድሮኖችንም እንዳያበሩ ወይንም እንዳይንቀሳቀሱ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግ ሲሆን ድሮንን ለተለያዩ አገልግሎቶች ለማዋልም ህጋዊ ስልጣን ካለው አካል ፈቃድ ማውጣት እንደሚቻል ተገልጿል።

በዚህ አጋጣሚ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የጥምቀት በዓል እንዲሆን ምኞቱን እየገለፀ ሕብረተሰቡ ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ ሰላምን የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለጸጥታ አካላት የተለመደ ጥቆማውን እንዲሰጥ ጠይቋል።