ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – በማእከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ በጭነት ተሸከርካሪ ተደብቆ ሲጓዝ የነበረ 123 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥን ጨምሮ ተተኳሽ ጥይቶችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ የመምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ውብነህ አስናቀ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው የተያዘው ዛሬ እኩለ ቀን በሳንጃ ከተማ የፍተሻ ኬላ ላይ ነው ብለዋል፡፡
ፖሊስና የጉምሩክ አባላት በጋራ ባደረጉት ጥብቅ ፍተሻ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-77550 ኢት በሆነ ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 123 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥና 250 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ተተኳሽ ጥይት ተይዟል።
የጦር መሳሪያውን ከምእራብ ጎንደር ዞን ምድረ ገነት ከተማ ወደ ደብረማርቆስ ከተማ ለማስገባት ታቅዶ ሲጓጓዝ እንደነበር ኮማንድሩ አስረድተዋል፡፡
ፖሊስ አሽከርካሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሀገርን ሰላምና የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ ወንጀል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመሆን ድርጊቱን ለመከላከል የጀመረው ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
የፊታችን ሰኞ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማደናቀፍ አንዳንድ የጥፋት ሃይሎች ሙከራዎች ሊያደርጉ እንደሚችሉ በመገመት ፖሊስ አስፈላጊውን የደህንነት ጥበቃና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ኮማንደሩ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።