በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የፌዴራሉ መንግስት ቁርጠኛ ነው – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

ታኅሣሥ 17/2015 (ዋልታ) በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የፌዴራሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ልኡክ ዛሬ መቐለ ገብቷል።

የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ልኡክ መቐለ አሉላ አባነጋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።

የፌዴራሉ መንግስት ልኡክ ከመቐለ ከተማ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችና የትግራይ ክልል አመራሮች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው ውድመትና የደረሰው ችግር እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ፣ ህዝቡም በምግብ እና በመሰረታዊ አቅርቦት እጥረት ከባድ ችግር ውስጥ እንደወደቀ የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

የፌዴራሉን መንግስት ወክለው የሄዱ የተለያዩ ተቋማት አመራሮችም በትግራይ የደረሰውን ውድመት የሚመጥን የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ ስራ እየተሰራ መሆኑንና ይህንንኑ በአጭር ጊዜ ለመተግበር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የፌዴራሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም የልዑኩ መሪ አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።