የካቲት 17/2014 (ዋልታ) በአውሮፓ ኅብረት የ19 ሚሊየን 250 ሺሕ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ለ3 ዓመታት የሚተገበር መፍትሄ ለማሕበራዊ ጤና ተግዳሮቶች በሥርዓተ ጾታና እኩልነት ላይ የሚሰራ ፕሮጀከት በአራት ክልሎች ይፋ ተደርጓል፡፡
ፕሮጀከት በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች በተመረጡ 15 ወረዳዎች ነው የሚተገበረው፡፡
በሶማል ክልል ይፋ በተደረገው ፕሮግራም ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ፕሮግራሙ በእናቶች፣ ህጻናትና ሴቶች ላይ በተለይ በታዳጊ ልጃገረዶች እንዲሁም ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን ጤና ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ለማሳከት የቤተሰብ እቅድ፣ የሥርዓተ-ምግብ፣ የስነ-ተዋልዶ ጤና፣ የሃይጅን፣ የአከባቢና የግል ንጽህና እጠባበቅ ፕሮግራም እንዲሁም ጾታዊ ጥቃትን ለማስቆም ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
ለፕሮግራሙ ስኬት በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የሴክተር መስሪያ ቤቶች ቅንጅትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ የቴክኒክ ድጋፍ በአውሮፓ አግሪ አማካሪ ድርጅት ሚሸፈን ሲሆን የእውቀት ጥናትና ምርምር ሥራው ደግሞ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሰራ መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡