ከተማ አስተዳደሩ ለሶማሌ ክልል ለእንስሳት መኖ የሚሆን ድጋፍ አደረገ

የካቲት 17/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለእንስሳት መኖ የሚሆን ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ አስረክበዋል።

የሶማሌ ክልል ሕዝብ የተከሰተበት ድርቅ ከፍተኛ ቢሆንም ችግሩን ለመቆጣጠር እያደረገው ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ሆኖም በክልሉ አቅም ብቻ የምንቆጣጠረው ስላልሆነ ለወንድሞቻችን ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተከሰተብን ከፍተኛ ድርቅ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለሶማሊያ ክልል ሕዝብ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢትዮጵያ የተጋረጠባት የኅልውና አደጋ ለመመከት በአማራና በአፋር ክልል እንዲሁም የተለያዩ የድርቅ አደጋዎች ለተከሰተባቸው አካባቢዎች እስካሁን ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

በሳራ ስዩም