በ2014 የትምህርት ቤቶች ክፍያ አተገባበር

መስከረም 18/2014 (ዋልታ) ለሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መደበኛው የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ በነባሩ የአስር ወር ክፍያ ሥርዓትን ተከትሎ እንደሚተገበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና፣ ጥራት፣ ሙያ ብቃት፣ ማረጋገጫ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መደበኛው የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ1987 ዓ.ም ባወጣው አዋጅ ቁጥር የ206/87 መሰረት በነባሩ የአስር ወር ክፍያ ሥርዓትን ተከትሎ በትምህርት ዓመቱ ሙሉ እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡

ምክትል ስራ አስኪያጇ ነባሩና ለረጅም ዓመታት በሀገሪቷ ሲተገበር የኖረው የአስር ወር የትምህርት ክፍያ ሥርዓት ለአንድ የትምህርት ዘመን አስር ወር ክፍያ የሚል እንደሆነ ተናግረው፣ በተያዘው 2014 ዓመትም ይህንን የአከፋፈል ሥርዓት ተከትሎ የሚፈፀም ይሆናል ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል፡፡