የካቲት 24 / 2013 (ዋልታ) – በመንገድ ትራፊክ አደጋ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ 1 ሺህ 849 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ495 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል።
በመንገድ ትራፊክ አደጋ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ 1 ሺህ 849 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ495 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
ከሐምሌ 1 ቀን 2012 እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ 20 ሺህ 672 የመንገድ ትራፊክ አደጋ ደርሷል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት የወንጀልና ትራፊክ መረጃ ትንበያ ተወካይ ዲቪዥን ሃላፊ ኢንስፔክተር መስፍን አይተነው እንደገለጹት፣ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ከጠፋው ህይወትና ከወደመው ንብረት ባሻገር በ2 ሺህ 646 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን 2 ሺህ 565 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ለቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
495 ሚሊየን 240 ሺህ 473 የሚገመት ንብረት በመንገድ ትራፊክ አደጋው መውደሙን የተናገሩት ኢንስፔክተር መስፍን፤ ሪፖርቱ የትግራይ ክልልን እንዳላካተተ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የትራፊክ አደጋ መረጃ እንዳልደረሰ አመልክተዋል።
ከተመዘገበው የትራፊክ አደጋ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 15 ሺህ 844 የትራፊክ አደጋ መድረሱንና 192 ሰዎች በአደጋው ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውን ጠቁመዋል።
“በ846 ሰዎች ላይ ከባድ፣ በ512 ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብለዋል፡፡
የመንገድ ትራፊክ አደጋውም በአሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር ጉድለት፣ ቸልተኝነት እና ብቃት ማነስ፣ በተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት፣ ወቅቱን የጠበቀ የቦሎ እድሳት ባለማድረግ፣ በመንገድ ግንባታ ችግርና በእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ችግር እንደሚከሰት ኢንስፔክተር መስፍን መጠቆማቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።