ጥር 24/2015 (ዋልታ) በግማሽ በጀት ዓመቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን 2 ነጥብ 34 ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር ቤት መላካቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ለውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርቧል፡፡
በዚህም በመንፈቅ ዓመቱ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን በማጠናከር፣ የዜጎችን መብት በማስከበርና የዲያስፖራውን ማህበረሰብ የልማት ተሳትፎ በማጎልበት ረገድ ሰፊ ስራ መሠራቱን አስታውቋል፡፡
ከዚህም ውስጥ ከህወሓት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍተሄ መስጠት እንደሚቻል ያመላከተ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ውጤት መሆኑን ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ አንስቷል።
በዓመቱ ከ102 ሺሕ በላይ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ታቅዶ እስካሁን ከ51 ሺሕ በላይ የሚሆኑትን መመለስ መቻሉንም ተገልጿል።
ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች መተግበራቸው፣ ከህወሓት ጋር የተደረሰው የሠላም ስምምነት እና የተቋሙን በሰው ኃይል ማደራጀት በጠንካራ ጎን የተነሳ ሲሆን የጸጥታ ችግር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተግዳሮትነት ተነስቷል።
በቃልኪዳን ሀሰን