ኢኳቶሪያል ጊኒ በታሪኳ የመጀመሪያዋን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች

ጥር 24/2015 (ዋልታ) በምዕራብ አፍሪካ የአትላንቲክ ውቂያኖስ ዳርቻ ላይ የምትገኘው ኢኳቶሪያል ጊኒ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሾማለች፡፡

ሮኪ ቦቲ አዲሷ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቴዎድሮ ኦቢያንግ አስታውቀዋል፡፡

ቦቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የእሳቸው መሾም በሀገሪቱ ሴቶች በፖለቲካው ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያነቃቃ ነው ተብሏል፡፡

እንደቢቢሲ ዘገባ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቴዎድሮ ኦቢያንግ እ.ኤ.አ ከ1979 ጀምሮ ሀገሪቷን ለ44 ዓመታት የመሩ ሲሆን በቀጣይ ስልጣኑን ለልጃቸው ለማስተላለፍ እቅድ አላቸው በሚል ይተቻሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ልጃቸው ቴዎድሮ ኑጉማ ኦቢያንግ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን ከወዲሁ ራሳቸውን ለፕሬዝዳንትነት እየሞሸሩ እንደሆነ ይነገራል፡፡