ታኅሣሥ 25/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ወረዳ የበጋ መስኖ የስንዴ እርሻን አስጀመረ።
በክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ኃላፊ ኤሊያስ ከድስ በአሁኑ ወቅት ዘንድሮ የበጋ የመስኖ ስንዴ ምርት ከዞኑ የግብርና ቢሮ ጋር በመሆን የአካባቢውን አርሶ አደር ግንዛቤ በማሳደግ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ዘንድሮ እንደ ክልል በተጀመረው የበጋ የመስኖ ስንዴ እርሻ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን የገለጹት ኃላፊው በዞኑ ከ35 ሺሕ ሄክታር በላይ በዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የገለፀው የዞኑ የግብርና ቢሮ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የአካባቢው መሬት ለም ቢሆንም ከፍተኛ ጉልበት ያላቸውን ትራክተሮችን ለማስገባትም እየተሰራ ነው ተብሏል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች ባዩት ለውጥ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረው ከዚህ ቀደም ያገኙ ከነበረው ምርት በዘንድሮው የተሻለ እንደሚያገኙ ተስፋ እንዳላቸው አንስተዋል።
የተጀመረው የበጋ የመስኖ እርሻ በህይወታቸው ትልቅ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው የትራክተር ችግር ግን አለብን ሲሉ አመልክተዋል።
ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው ያሉት የደቡብ ምእራብ ዞን አስተዳደር ታዬ ጉዲሳ አሁን ወደ ኢንቨስመንት የተሸጋገሩትን በማስተባበር አየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚልኪያስ አዱኛ (ከወሊሶ)