ሰኔ 4/2014 (ዋልታ) ባህል በማኅበረሰቡ ዘንድ መልካም ገፅታና የአብሮንት እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ የጎላ ሚና እንዳለው ተጠቆመ።
የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም 9ኛው ሀገር ዐቀፍ አውደ ጥናት የተለያዩ ምሁራንና እንግዶች በተገኙበት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
“ባህል ለሰላም እና ብሔራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው አውደ ጥናቱ እየተካሄደ የሚገኘው።
የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ መልካሙ በዛብህ (ዶ/ር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በሰላም አብሮ ለመኖርና ለመግባባት የአንዱን ባህል ለሌላው ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባህል በማኅበረሰቡ መልካም ገፅታና የአብሮንት እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ባህላዊ እርቅን ጨምሮ ሌሎችም እሴቶችን ማጠናከር ያስፈልጋልና አውደ ጥናቱ በዚህ ጊዜ መካሄዱ ወቅቱን የጠበቀ ነው ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባህል ለኢኮኖሚና ማኅበራዊ እድገት ያለውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በአውደ ጥናቱ ባህል ተኮር ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የሚካሄድባቸው ሲሆን የደራሲ አበረ አዳሙ “አገሬን አፋልጉኝ” እና “ወንበዴው መነኩሴ” የተሰኙ ሁለት የመጻሕፍት ምርቃትም የመርኃግብሩ አካል ናቸው።
ትዕግስት ዘላለም (ከደብረ ማርቆስ)