ባለስልጣኑ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ

ሰኔ 22/2014(ዋልታ) የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን አስጠነቀቀ፡፡

በቀን ከዘጠኝ ሚሊየን ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ቢሆንም ተጠቃሚው ዘንድ በወቅቱ እየደረሰ አለመሆኑንም ነው ባለስጣኑ የገለጸው፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን የነዳጅ ስታንዳርድ ጥናት ዳይሬክተር ለሜሳ ቱሉ ነዳጅ የጫኑ የአቅራቢ ድርጅቶች ቦቴ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የመዘግየት ችግር መኖሩን ጠቁመው ነዳጅ የጫኑት ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የሚዘገዩበት ምክንያትም ዋጋ ከዛሬ ነገ ይጨምራል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አዲስ ዋጋ ሲታወጅ በሚኖረው ልዩነት ለማትረፍ በመፈለግ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደዚህ ዓይነት ችግር ከመፍጠር በማይቆጠቡ የነዳጅ አቅራቢዎች ላይ ማደያን ከማሸግ ንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ነዳጁ በወቅቱ ተጠቃሚ ዘንድ እንዲደርስ ለማስቻል ከመነሻ እስከ መድረሻ ባለው የማጓጓዝ ሂደት ከየክልሎች የንግድ ቢሮዎች ጋር በመተባበር የክትትልና ቁጥጥር ስራ  እየተከናወነ መሆኑን ኃላፊው ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ገልጸዋል።

በተጠቃሚው በኩል ደግሞ ነዳጅ በሚቀጥለው ወር ሊጨምር ይችላል በሚል በየአካባቢው በበርሜልና በሮቶ በድብቅ የማከማቸት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ብለዋል።

4 እና 5 ማደያ ያላቸው ኩባንያዎች በአንዱ ብቻ አገልግሎት እያቀረቡ ሌላኛው ላይ አገልግሎት ያለመስጠት ክፍተት ይስተዋላል ያሉት ኃላፊው፤ ይህም የትራንስፖርት አገልግሎቱ ቀልጣፋ እንዳይሆን ማነቆ መሆኑን ገልጸዋል ።

በአፋር ክልል ነዳጅ ጭነው ተደብቀው የነበሩ 15 ቦቴዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቀሱት ለሜሳ፤ ክልሉ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል።

ነዳጅ በማጓጓዙ ሂደት ከአዋሽ ጀምሮ ያለውን የተሽከርካሪ መዘግየት ለማስቀረት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ተመድበው ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺህ 200 ማደያዎች አሉ ያሉት ኃላፊው የነዳጅ ስርጭቱ ፍትሃዊ እንዲሆን በየአካባቢው ያሉ የንግድ ቢሮዎች ቁጥጥር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ተሽከርካሪዎችን መመለከት የተለመደ ሆኗል።

ይህን ለማስተካከል የአቅርቦት ችግር የለም ያሉት ኃላፊው በየከተማው ያሉ የንግድ ቢሮዎች ቁጥጥራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።