ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ውሳኔ ሰጭነት እንዲከበር እንደሚሰራ ገለጸ

ሰኔ 22/2014(ዋልታ) ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ሰጭነት እንዲከበር እንደሚሰራ ገለጸ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አንደኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች በራሳቸው ጉዳይ ተወያይተው የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የኢትዮጵያ ሴቶች ለፍትህ እና ነጻነት ያደረጉት ትግል የጎላ ቢሆንም ተገቢውን ውክልና ሳያገኙ ቀርተዋል ነው ያሉት።

ጉባኤው በመዝጊያው በሚያደርገው የአመራር ምርጫ ለሴቶች ትግል የጎላ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አመራሮችን እንደሚመርጥ ይጠበቃልም ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ ሴቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ጠንካራ ፖለቲካዊ አመራርን ፣ ሀገራዊ አንድነትን እና ድህነት መታገያ መንገዶችን ለትውልድ የሚያወርሱ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ሴቶች የሀገር ኅልውና ዘመቻ ላይ ግንባር ቀደም ሆኖ በመዝመትና ስንቅ በማቀበል ያደረጉት ተሳትፎ አይረሳም ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ሊጉ በሀገራዊ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ተሳትፊ ሴቶችን ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።

የሴቶች ሊግ የመጀመሪያ ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን በነገው ዕለት የሊጉን ከፍተኛ አመራሮች ምርጫ እና ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

እንየው ቢሆነኝ (ከሀዋሳ)