ባይደን ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ላይ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳትጠቀም አስጠነቀቁ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

መስከረም 7/2015 (ዋልታ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ የኬሚካልም ይሁን የታክቲካል ኒውክሌር ጦር መሣሪያ በዩክሬን ጦርነት ላይ እንዳትጠቀም አስጠነቀቁ።

ባይደን ከሲቢኤስ ቴሌቪዥን ጋር ባረደጉት ቆይታ የኒውክሌር መሣሪያ መጠቀም “ጦርነትን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ይቀይረዋል” ብለዋል።

የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ቢውል አገራቸው ምን እርምጃ እንደምትወስድ ግን የገለጹት ነገር የለም።

ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸውን የኒውክሌር ኃይል “በተጠንቀቅ” እንዲቆም ማዘዛቸው ይታወሳል።

ይህንን ያደረጉት “ከምዕራቡ ዓለም ማስፈራሪያዎች” ስለሚወጡ እንደሆነ ገልጸዋል።

ላለፉት 80 ዓመታት ዓለም ላይ የቆዩትን የኒውክሌር መሣሪያዎች አንዳንድ አገራት እንደ ደኅንነታቸው ማረጋገጫ ይቆጥሯቸዋል።

የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ፌደሬሽን እንደሚለው ሩሲያ 5 ሺሕ 977 ገደማ ከኒውክሌር ኃይል ጋር የተያያዙ መሣሪያዎች አሏት። መሣሪያዎቹን ትጠቀማለች ተብሎ ግን አይጠበቅም።

ታክቲካል ኒውክሌር በመባል የሚታወቁት የአጭር ርቀት መሣሪያዎች ሲሆኑ ስትራቴጂክ ኒውክሌር ደግሞ የረዥም ርቀት ተስወንጫፊ መሣሪያዎችን ያካትታል።

ዩክሬን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ800 ሺሕ ሄክታር በላይ የሚሆን ግዛት ከሩሲያ መልሳ እንደገና መቆጣጠሯን ገልጻለች። ይህም ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዩክሬን ያስመዘገበችው ከፍተኛ ስኬት ነው ተብሏል።

ፑቲን በበኩላቸው የዩክሬን የቅርብ ጊዜ ድል ኦፕሬሽናቸውን እንደማይገታው መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!