የካቲት 11/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ቤተ እምነቶች ለተከታቶቻቸው የሰላምን አስፈላጊነት ማስተማር ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶች እንደገለጹት በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖትና ብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶች በስፋት እየተስተዋሉ መጥተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች እየተባባሱ ለበርካታ ሰዎች ሞትና ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ምክንያት መሆናቸውን አስታውሰው ድርጊቱ በየትኛውም ሃይማኖት የሚወገዝና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።
እንዲህ አይነት ድርጊቶች የሚፈፀሙት በእምነትና ማንነት ሰበብ የጥፋት ዓላማ በያዙ ግለሰቦች በመሆኑ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ሊቀበለው አይችልም ነው ያሉት አባቶቹ።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ቤተ እምነቶች ለተከታቶቻቸው የሰላምን አስፈላጊነት ማስተማር ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።