የመንግሥታቱ የልማት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች አሸባሪው በደቡብ ወሎ ዞን ያደረሰውን ጉዳት ተመለከቱ

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ዋና ኃላፊ ቱርሃን ሳልህና ሌሎች የልማት ድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች አሸባሪው ትሕነግ በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ያደረሰውን ጉዳት ተመለከቱ።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ለልዑክ ቡድኑ አሸባሪው እስካሁን በተደረገ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን እና ከፍተኛ መጠን ያለው ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።

ይህም ውድመት በርካቶች የሥነ ልቦና ጉዳትና ጫና እንዲደርስባቸው ማድረጉን አስረድተዋል።

አካባቢውን መልሶ ለማቋቋም ተደጋግፎ መስራት አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውንም የደቡብ ወሎ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ዋና ኃላፊ ቱርሃን ሳልህ በበኩላቸው በዞኑ የቀረበላቸው ሪፖርት በአግባቡ የተደራጀና እውነታውን ገላጭ ስለመሆኑ ጠቁመው በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን አስታውቀዋል።

የተቋረጡ የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲጀምሩና በዋናነት በሴቶች ተሳትፎ የሚንቀሳቀሱ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መልሰው እንዲቋቋሙ የማድረግ ሥራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

አክለውም ከሰላም፣ ፍትሕና ደኅንነት አኳያ የደረሰውን ጉዳት ሊቀይር የሚችልና በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ ድጋፍን ድርጅታቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል።