ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል

መስከረም 20/2015 (ዋልታ) የ2015 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ እንደሚጀመር ተገለጸ።

ወልቂጤ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የፕሪሚየር ሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ባህር ዳር ከተማ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከተመለሰው ኢትዮ-ኤሌትሪክ ጋር ከቀኑ 10 ሰአት ይጫወታሉ።

ነገ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ኢትዮጵያ መድን ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 7 ሰአት እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት እንደሚጫወቱ ተመላክቷል።

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተሳተፈ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በሁለተኛ ዙር ከቱንዚያው ሴፋክሲያን ጋር የሚያደርገውን የደርሶ መልስ ጨዋታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሊጉ መርኃ ግብር ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎበታል።

የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር መርኃ ግብሮች በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም (ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ሳምንት)፣ በድሬዳዋ ስታዲየም (ከስድስተኛ እስከ 10ኛ ሳምንት) እና በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ሜዳ (ከ11ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት) ይከናወናሉ።