ብልጽግና ፓርቲ በሐረሪ ክልል የምርጫ ምልክቱን እና ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ

 

በሐረሪ ክልል የምርጫ ምልክት

የካቲት/ቀን 2013 (ዋልታ) – ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱን እና ማኒፌስቶውን በሐረሪ ክልል ይፋ አደረገ።

ፓርቲው በሐረሪ ክልል ምልክቱን እና ማኒፌስቶውን ይፋ ያደረገው አባላቱና ደጋፊዎቹ በተገኙበት “ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ በተዘጋጀው የስብሰባ መድረክ ነው።

በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ሐላፊ አቶ አብዱልጀባር መሐመድ እንደተናገሩት፤ ፓርቲው ሰላም የሰፈነባት እና የበለጸገች ኢትዮዽያን ለመገንባት ይሰራል።

”በለውጥ ምህዋር ውስጥ መጓዝ ከጀመርንበት ሶስት ዓመታት ውስጥ ብዙዎችን ያስደመመ ተጨባጭ ተግባራት ተከናውነዋል” ብለዋል።

“ከለውጡ በተጻራሪ የቆሙ ሂደቱን ለማደናቀፍ ቢሞክሩም ለውጡ ይበልጥ ጎልቶና ጎልብቶ በፍጥነት እየገሰገሰ ይገኛል” ያሉት አቶ አብዱልጀባር፤ ብልጽግና ከግልና ጊዜያዊ ፍላጎት የራቀ ለህዝቦች ሁለንተናዊና ዘላቂ ተጠቃሚነት በመትጋት ለዜጎች እንደ አምፖል የሚበራ ፓርቲ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፓርቲው በእውነትና እውቀት ላይ የተመሰረተ በመደመር እሳቤ እየተመራ የመግባባት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እየገነባ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫዎችን በመቀየስ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑም ተናግረዋል እንደ ኢዜአ ዘገባ ።

“ከሁሉም በላይ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ በመወዳደር ማሸነፍ እንዲቻል ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በትብብር በመስራት ምርጫው ነጻ፣ ሠላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲሳካ ሃላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣለን” ብለዋል።

የክልሉ ነዋሪ በፓርቲው የተመዘገበውን ተጨባጭ ለውጥ በመገንዘብና አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሻግረውን የፓርቲውን እቅድና ራዕይ በመመልከት ብልጽግና ፓርቲን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።