ብልጽግና ፓርቲ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ብሔራዊ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገለጸ

ጥቅምት 7/2015 (ዋልታ) ብልጽግና ፓርቲ 20ኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ብሔራዊ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገለጸ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የ20ኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ብሔራዊ ጉባዔን አስመልክቶ መልካም ምኞታቸውን ለቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ዥንፒንግ፣ ለመላው አመራር እንዲሁም ለፓርቲው ዋና ፀሀፊ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በሺ ጂንፒንግ መሪነት ጥራት ያለው እና ፈጠራ የታከለበት እድገት በማስመዝገብ በርካታ ሕዝብ ከድህነት ማውጣት መቻሉን የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሸኤቲቭ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራትን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ፓርቲው በጉባዔው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ለቻይና ብቻ ሳትሆን ለመላው ዓለም ተጽዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሲፒሲ በ20ኛ ጉባዔውም ለዓለም ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግና ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አመርቂ ውጤቶችን በተለያዩ ዘርፎች ማስመዝገቡን ገልጸው ወደ ፊትም የብልጽግና እና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲዎች ግንኙነትን በማጠናከር የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ፓርቲያቸው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ጉባኤው የተሳካ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW