ብልጽግና ፓርቲ የአገሪቱን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚሰራ ገለጸ

መጋቢት 6/2014 (ዋልታ) ብልፅግና ፓርቲ በቀጣይ ውስጣዊ ሥነ ምግባርን በማጠናከር የአገርን ክብር ባስጠበቀና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያስከብር አኳኃን ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታውቋል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰጡት መግለጫ ገዥው ፓርቲ በቀጣይ ጠንካራ ጎኖቹን በማጠናከርና ጉድለቶቹን በማረም እንደሚሰራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

ብልፅግና ውስጠ ፓርቲ አንድነቱን በማጠናከር የአገሪቱን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ለ50 እና ለ60 ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የዜጎች ጥያቄም በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ እንዲፈቱ ለማስቻል ብልፅግና ከሕዝብ ጋር ይሰራል ያሉት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የተጀመረው አካታች የምክክር መድረክም በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ እንደ መሪ ፓርቲ ብልፅግና ኃላፊነቱን በአግባቡ እንደሚወጣ ገልጸዋል።

ፓርቲው የምክክር መድረኩን ሌሎች አካላት እንዳያሰናክሉት እንደሚከላከል ያስታወቁት ምክትል ፕሬዝዳንት ደመቀ መኮንን በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍና መልሶ ማቋቋም የፓርቲው የቀጣይ የቤት ሥራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዲፕሎማሲው ረገድም ካለፉት ስኬቶች ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበት ደካማ አካሄዶችን በማረም እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ እንደ ገዢ ፓርቲ ብልፅግና በቀጣይ ለዜጎች ፍትሃዊነት፣ እኩልነት እና አንድነት እንዲሁም ለአገር ልዕልና ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሶ ጉባኤው መጠናቀቁን በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

በደምሰው በነበሩ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW