ብልፅግና ፖርቲ ጽህፈት ቤት የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን አከበረ

ኅዳር 23/2015 (ዋልታ) የብልፅግና ፖርቲ ጽህፈት ቤት 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን አከበረ።

የብልፅግና ፖርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ ህዝቡ  በህገ-መንግስቱ ያለውን ግንዛቤና እምነት ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከልዩነት ይልቅ የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች የሚልቁ በመሆናቸው ቀኑ በልዩነት ውስጥ አንድነትን እንድናጠናክር ይረዳናል ብለዋል።

“ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ የተፈፀመው የሰላም ስምምነት ዘላቂ እንዲሆን ያግዛልም ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላሟን አፅንታ እንድትቀጥል የብልፅግና ፖርቲ አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ የድርሻውን ይወጣል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የመራራቅ አጀንዳ ቀርፀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ቢበረክቱም ያልተረጋጋች፣ መርህና መሪ የሌላት ሀገር እንድትሆን ቢሰሩም ኢትዮጵያ እነዚህን ኃይሎች ድል አድርጋ ቀጥላለች ብለዋል።

በዙፋን አምባቸው