የካቲት 16/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእስካሁኑ ሂደት በ673 የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁስ መጓጓዙን አስታወቀ።
በየደረጃው የሚገኙ የክልል አመራሮች ለምርጫ ቁሳቁስ ማጓጓዣ እንዲተባበሩ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች የምዝገባ መረጃና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር እየተወያየ ነው።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በውይይቱ ቦርዱ በመራጮች መረጃ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና በምርጫ ቁሳቁስ ማዳረስ እስካሁን ያከናወናቸውን ሥራዎች አብራርቷል።
በእስካሁን ሂደት በ673 የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁስ መጓጓዙን አስታውቋል።
በ50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ እየተጓጓዘ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል።
ሰብሳቢዋ የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለማድረስ የማጓጓዣ ችግር መኖሩን ጠቅሰው በየደረጃው የሚገኙ የክልል አመራሮች ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ቦርዱ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በእነዚህና እስካሁን ባጋጠሙ ሌሎች ችግሮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።