የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በሰባት ወራት 26.7 ቢሊየን ብር ሰበሰበ

የካቲት 16/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ሰባት ወራት 26 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ቢሮው የከተማ አስተዳደሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነና የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ በተገኙበት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።

ከታክስ ከፋዩ ማኅበረሰብ ጋር ያለው ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጸው ቢሮው ግብር አሳውቆ በወቅቱ የመክፈል ተሳትፎ እያደገ ነው ብሏል።

በተያዘው የግብር መክፈያ ዓመት ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሠራ መሆኑንና ያለፉት ወራት አፈጻጸምም የተሳካ መሆኑ ተጠቁሟል።

በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት 26 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ነው የተባለው።

የቢሮው የሰባት ወራት አፈፃፀም ከዓመቱ ዕቅድ አኳያ ሲመዘን 62 ነጥብ 59 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ የቢሮው የገቢ አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ታዬ ማስረሻ ገልፀዋል፡፡

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከ1997 እስከ 2007 ዓ.ም መከፈል የነበረበት ግብር እና ክፍያውን ላልፈፀሙ 141 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ምህረት መደረጉ ይታወሳል፡፡
(ምንጭ ፡-ኢዜአ)