ቦርዱ የመቀመጫ እንዲሁም የምርጫ ክልል ለውጦችን እንደማይቀበል አስታወቀ

                         የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች የመቀመጫ እንዲሁም የምርጫ ክልል ለውጦች እንደማይቀበል አስታውቋል።

የመቀመጫ ወይም/እና የምርጫ ክልል ለውጦችን በማከናውን በዚያ መሠረት ምርጫ እንዲፈጸምላቸው ከጠየቁ ክልሎች/የከተማ መስተዳድሮች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ይገኙበታል ብሏል።

የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም አንቀጽ 7(4) መሠረት የመቀመጫ ለመቀየር የሚሰጡት ውሳኔ ከእጩዎች ምዝገባ 6 ወራት አስቀድሞ መሆን እንደሚኖርበት ይደነግጋል ሲል ምርጫ ቦርዱ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ የምርጫ ሥራዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም በተገቢው ወቅት ለማጠናቀቅ ክልሎች/ከተማ መስተዳድሮች ስድስት ወራት ቀድመው ለውጦቻቸውን ማስገባታቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሷል።

በመሆኑም በአዋጁ በተቀመጠው መሠረት ከእጩዎች ምዝገባ 6 ወራት አስቀድሞ ያልቀረበ ማንኛውንም የምክር ቤት መቀመጫ እና የምርጫ ክልል ለውጥ ቦርዱ እንደማያስተናግድ አስታውቋል።

ቦርዱ የ2007 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ በተከናወነበት የመቀመጫ ብዛት እና የምርጫ ክልል መሠረት 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ የሚያስፈጽም መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማከናውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጎ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለፌደራል እና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች እንዲሁም ለአዲስ አበባ እና ለድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች ግንቦት 28 እና ሰኔ 05 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ እንደሚካሄድ አሳውቆ እየሰራ እንደሚገኝ ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።